ትልቁ ሰማያዊ አውቶቡስ በዘገየ ጊዜ
Mecelin Kakoro
Mango Tree

በቀን አንድ ጊዜ ትልቁ ሰማያዊ አውቶብስ ወደ ከተማ የሚሄዱ ሰዎችን ለመውሰድ እነቡቡ መንደር ይቆማል። ቡቡ እንደዚህ ያለ ትልቅ አውቶቡስ አይቶ አያውቅም። ቡቡ ዘጠኝ የተሳፋሪ መስኮቶችን እና አንድ የሾፌር መስኮት ይቆጥራል፡፡ ‹‹ቢያንስ 6 መቀመጫዎች በአንድ ረድፍ ያሏቸው 9 ረድፍ የተሳፋሪ መቀመጫዎች አሉት ማለት ነው›› ሲል ያስባል ቡቡ።

ቡቡ ትክክል ከሆነ፣ ትልቁ ሰማያዊ አውቶብስ ምን ያህል መንገደኞችን ማሳፈር ይችላል?

1

ነገ እናቱ አዲስ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ልትገዛለት ቡቡን ወደ ከተማ ትወስደዋለች። ደርዘኑን እንቁላል 15 ብር ትሸጣለች። ብዙ ጊዜ በሳምንት 450 ብር ታገኛለች። 450 ብር ለማግኘት ስንት ደርዘን እንቁላል መሸጥ ይኖርባታል? ለቡቡ አዲስ ዩኒፎርም ለመግዛት የሚያስችላትን ገንዘብ መቆጠብ የቻለችው ላለፉት 4 ሳምንታት ከሸጠችው ገንዘብ ግማሹን በመቆጠብ ነው፡፡

በ 4 ሳምንታት ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እንዳጠራቀመች ማወቅ ትችላላችሁ?

2

ቡቡ የአውቶቡስ ጉዞ ካደረገ ሦስት ወር ሊሆነው ነው። ለመጓዝ በጣም ጓጉቷል!

ነገ የሚጠብቀው ቀን ነው። አንድ ሰዓት ሲል አልጋ ላይ ነው፣ ነገር ግን እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። አእምሮው እየሮጠ ነው። ስለ ከተማ ጉዞው ማሰቡን ሊያቆም አልቻለም። ሦስት ተኩልም ላይ ቡቡ ዓይኖቹ ፍጥጥ እንዳሉ ናቸው።

3

ሁል ጊዜ ጠዋት እናቱ ቡቡን አንድ ሰዓት ላይ ከእንቅልፉ ትቀሰቅሰዋለች። ትናንት ሌሊት ግን አምስት ሰዓት ድረስ ዘግይቶ ቢተኛም ዛሬ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ነቅቷል::

እስከ አንድ ሰአት ድረስ ታጥቦና ለብሶ ለመሄድ ተዘጋጅቷል። ቡቡ ትናንት ማታ ለምን ያህል ጊዜ ተኝቷል?

4

ለሁለት ሩብ ጉዳይ ሲል ቡቡ እና እናቱ አውቶቡስ ማቆሚያው ቦታ ደረሱ። ትልቁ ሰማያዊ አውቶቡስ ሁለት ሰዓት ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡቡ እናት ሰዓቷን ትመለከታለች። ትልቁ ሰማያዊ አውቶቡስ አስራ አምስት ደቂቃ ዘግይቷል። ‹‹እስከዛሬ ግን አውቶቡሱ ሁልጊዜ በሰዓቱ ይደርስ ነበር። ምን ሆኖ ይሆን?›› ትላለች።

5

ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ሰዎች ወደ አውቶቡስ ማቆሚያ መጡና ተቀላቀሉ። እነሱም እንዲሁ ሰዓታቸውን እየተመለከቱ አውቶቡሱ ለምን እንደዘገየ ይጠይቃሉ። ‹‹አሁን ሦችት ሰዓት ነው፡፡ ለስራ ሊረፍድብኝ ነው!›› ይላል ሰማያዊ ሙሉ ልብስ የለበሰው ራሰ በራ ሰውዬ።

ቡቡ እና እናቱ ለረጅም ጊዜ ሲጠብቁ ቆይተዋል። ለቡቡ፣ ልክ ረጅም ሰዓት የቆመ ያህል ይሰማዋል። ግን ይህን ያህል አልቆየም፡፡ ምን ያህል ጊዜ የጠበቁ ይመስላችኋል?

6

ቡቡ ተጨንቋል። ‹‹እንዲያው የደንብ ልብሴን አገኝ ይሆን?›› በማለት እናቱን ይጠይቃል።

ቡቡ ወደ ከተማ የሚደረገው የደርሶመልስ ጉዞ 4 ሰዓት ያህል እንደሚወስድ ተረድቷል። እዚያ ለመድረስ አንድ ሰዓት፣ ለመገበያየት 2 ሰዓት እና ለመመለስ 1 ሰዓት። ‹‹ስምንት ሰአት ላይ ከጓደኞቼ ጋር የእግር ኳስ ጨዋታ አለኝ:: አውቶቡሱ ቶሎ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያለዚያ በጊዜ ወደ ቤት አንደርስም።››

7

አሁንም ይጠብቃሉ። ቡቡ ማልቀስ ጀመረ። ከተሰለፉት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ወደ ቤታቸው ሄዱ። ሌሎች የእጅ ሰዓቶቻቸውን አየት ያደርጋሉ፡፡
‹‹እንታገስ። እርግጠኛ ነኝ አውቶቡሱ በቅርቡ ይመጣል›› ትላቸዋለች እናቱ። ‹‹ወደ ቤት መሄድ እፈልጋለሁ!›› በማለት ቡቡ ያለቅሳል፡፡ ‹‹አስር ደቂቃ ብቻ›› አለችው። ‹‹አውቶቡሱ ሦስት ሰዓት ተኩል ስኪሆን ካልመጣ ወደ ቤታችን እንሄዳለን›› አለች፡፡

8

ያኔ አውቶብሱ እየጮኸ ሲመጣ ይሰማሉ። የቡቡ እናት ‹‹አየህ፣ ነግሬህ አልነበር›› ትላለች። ‹‹ልክ ሦስት ሰዓት ተኩል ሆኗል፣ ገበያችንን በፍጥነት እንገበያለን፡፡ አውቶቡሱ በሰዓቱ ከከተማ ከወጣ፣ ከእግር ኳስ ጨዋታህ በፊት እቤታችን እንደርሳለን።››

ቡቡ እንባውን ያብሳል። እግሩ ታመመ። ድካም ይሰማዋል። አውቶቡሱ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ቸኮለ።

9

የሚገርመው ነገር የመጣው ትልቁ ሰማያዊ አውቶቡስ አይደለም። ትንሽ ቀይ አውቶቡስ ነው። ቡቡ አውቶቡሱን ከጎን ሲያየው 4 የመንገደኞች መስኮቶችን ብቻ ቆጠረ። ‹‹እማማ›› ይላል ቡቡ፡፡ ‹‹ይህኛው ከሰማያዊው አውቶቡስ በጣም ያንሳል፡፡ ወደ ከተማ ለሚሄዱት ለሁሉም ሰዎች የሚሆን ቦታ በጭራሽ አይኖረውም፡፡››

በቡቡ ሃሳብ ትስማማላችሁ? ትንሿ ቀይ አውቶብስ ምን ያህል መንገደኛ ማሳፈር እንደምትችል መገመት ትችላላችሁ?

10

‹‹ቡቡ አብዝተህ ትጨነቃለህ›› ስትል እናቱ ታሾፍበታለች። ‹‹ቢያንስ በዚህ ፌርማታ የምንጠብቀው ሁላችንም መቀመጫ እናገኛለን፡፡››

‹‹እንፍጠን፣ ቶሎ ወጥተን ደህናዎቹን መቀመጫዎች እንያዝ፡፡ ከሁሉም ለረጅም ጊዜ የጠበቅነው እኛ እኮ ነን!››

11

ቡቡ እና እናቱ ወደ አውቶቡሱ ገቡ። ከኋላቸው 9 ተጨማሪ ሰዎች ሰልፍ ይዘዋል፡፡ ‹‹ለሁላችንም የሚበቃ መቀመጫ ይኖር ይሆን?›› በማለት ቡቡ ይጠይቃል።

በአውቶቡሱ ላይ 4 ረድፍ መቀመጫዎች እንዳሉ አየ፡፡ በአንድ በኩል 2 መቀመጫዎች እና በሌላኛው በኩል 2 መቀመጫዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ስንት መቀመጫዎች አሉ? በወረፋው ውስጥ ያሉት ሁሉም ሰዎች መቀመጥ ይችላሉ?

12

ቡቡ እና እናቱ ከበሩ አጠገብ ያሉትን 2 የፊት መቀመጫዎች ያዙ። ከፊት ለፊታቸው ሰፊ ቦታ አለ፡፡ ወደ ዉጪ ለማየትም ጥሩ ቦታ ነው።

ቡቡ ወረፋውን የተቀላቀሉ 6 አዳዲስ ሰዎችን ቆጠረ። ‹‹በአጠቃላይ 17 ተሳፋሪዎች አሉ ማለት ነው›› ሲል አሰበ። ለእናቱ ‹‹እማማ ለሁሉም የሚበቃ ቦታ አለ›› አላት። ‹‹አንድ ሰው ብቻ ለመቆም ይገደዳል፡፡››
ቡቡ በትክክል ቆጥሯል?

13

አሁን አውቶቡሱ ሞልቷል። ሹፌሩ በሩን ዘግቶ መኪናውን አስነሳ። ዉጪ ጫጫታ አለ። ቡቡ እና ሌሎች ተሳፋሪዎች በመስኮት ወደ ዉጪ ይመለከታሉ።

ብዙ ሰዎች አውቶብሱ እንዳያመልጣቸው እየሮጡ ነው። ‹‹አቁመው! አቁመው! አስገባን›› ይላሉ። ግን ዘግይተዋል፡፡ ቡቡ እና እናቱ ላልተሳፈሩት ሰዎች አዘኑላቸው።

14

የቡቡ እናት ሹፌሩን ‹‹ ትልቁን ሰማያዊ አውቶቡስ ለምን ይዘህ አልመጣህም?›› በማለት ጠየቀችው፡፡ እሱም ‹‹ትላንት ተበላሽቶብኝ ነው›› ሲል መለሰላት። ‹‹ይህ ትንሽ ቀይ አውቶቡስ ብቻ ነው ያለን፡፡››
‹‹ግን ትተናቸው የመጣነው ሰዎችስ?›› ስትል ጠየቀችው የቡቡ እናት። ‹‹አትጨነቂ›› አላት ሹፌሩ ‹‹ዛሬ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ለመመላለስ እቅድ አለኝ።››

ቡቡ ሲናገሩ ያዳምጣል። ቁጥሮች በጭንቅላቱ ውስጥ ይመላለሳሉ።

15

ቡቡ መቀመጫዎቹን እንደገና ይቆጥራል፡፡ ‹‹ይህ አውቶብስ 20 ሰዎችን ይዟል፡፡ 16ቱ ተቀምጠው 4ቱ ቆመዋል፡፡››

‹‹አውቶቡሱ 100 ተሳፋሪዎችን ወደ ከተማ ለማጓጓዝ ስንት ጉዞዎች ማድረግ ይኖርበት ይሆን? 200 ወይም 150 ተሳፋሪዎችንስ?›› ብሎ ራሱን ይጠይቃል። መልሱን ማግኘት ትችላላችሁ?
ቡቡ ተደሰተ። በቅርቡ አዲሱን የደንብ ልብሱን ያገኛል። ከዚያም አውቶቡሱ ወደ ቤት ይወስዳቸዋል፤ ለእግር ኳሱም በገጊዜ ይደርሳል።

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ትልቁ ሰማያዊ አውቶቡስ በዘገየ ጊዜ
Author - Mecelin Kakoro
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Mango Tree
Language - Amharic
Level - Read aloud