ሲምበግዊሬ
Rukia Nantale
Benjamin Mitchley

ሲምበግዊሬ እናቷ ስትሞት ብስጭት ተሰማት። የሲምበግዊሬ አባት ለልጁ እንክብካቤ ለማድረግ የተቻለውን አደረገ። ቀስ በቀስ የሲምበግዊሬ እናት በሌለችበት ደስተኝነትን መልሰው እንዴት እንደሚያገኙ አወቁበት። በየዕለቱ ጠዋት ቁጭ ብለው ስለመጪው ቀን ይነጋራሉ። በየምሽቱም ራት አብረው ይሰራሉ። ሳህኖቹን ካጠቡ በኋላ የሲምበግዊሬ አባት የቤት ስራዋን በመስራት ያግዛታል።

1

አንድ ቀን የሲምበግዊሬ አባት ከወትሮው አምሽቶ መጣ። ‹‹የት ነሽ ልጄ?›› ሲል ተጠራ። ሲምበግዊሬም ወደ አባቷ ሮጠች። አባቷ የአንዲት ሴትዮ ይዞ መምጣቱን ስታይ ቀጥ ብላ ቆመች። ‹‹ልጄ፣ አንዲት ልዩ የሆነች ሴትዮ እንድትተዋወቂ እፈልጋለሁ። ይህች አኒታ ነች›› አለ ፈገግታ እያሳየ።

2

‹‹እንዴት ነሽ ሲምበግዊሬ? አባትሽ ስላንቺ ብዙ ነገር ነግሮኛል›› አለቻት አኒታም፡፡ ይሁን እንጂ አኒታ ፈገግታ አላሳየችም፤ ወይም የሲምበግዊሬን እጅ አልጨበጠችም። የሲምበግዊሬ አባት ደስተኝት ተሰማው። ሦስቱ አብረው ስለሚኖሩበት ሁኔታና ህይወታቸው እንዴት ጥሩ እንደሚሆን አወራ። ‹‹ልጄ፣ አኒታን እንደ እናት እንደምታያት ተስፋ አደርጋለሁ›› አላት።

3

የሲምበግዊሬ ህይወት ተቀየረ። ጠዋት ጠዋት ከአባቷ ጋር ለመቀመጥ ጊዜ እያጣች መጣች። አኒታ በርካታ የቤት ውስጥ ስራ ስለሰጠቻት ማታ ማታ የቤት ስራዋን ለመስራት በጣም ይደክማት ጀምር። ከእራት በኋላ ቀጥታ ወደ መኝታዋ መሄድ ልማዷ እየሆነ መጣ። የሚመቻት ብቸኛው ነገር እናቷ የሰጠቻት በቀለም ያበደ ብርድ ልብስ ነበር። የሲምበግዊሬ አባት የልጁን መከፋት ልብ ያለው አይመስልም።

4

ከጥቂት ወራት በኋላ የሲምበግዊሬ አባት ለተወሰነ ጊዜ ራቅ ብሎ እንደሚሄድ ነገራቸው። ‹‹ለስራ ጉዳይ መሄድ አለብኝ›› አላቸው። ‹‹እርስ በእርሳችሁ እንደምትደጋገፉ ግን እተማመናለሁ።›› የሲምበግዊሬ ፊት ቅይርይር አለ፤ አባቷ ግን ይህን ልብ አላለም። አኒታ ምንም ቃል አልወጣትም። እርሷም ደስተኝነት አልተሰማትም ነበር።

5

ለሲምበግዊሬ ነገሩ ሁሉ እየከፋ ሄደ። ስራዎቿን ካልጨረሰች ወይም ካማረረች አኒታ ትመታታለች። በእራት ሰዓትም ሴትዮዋ ብዙውን ምግብ ስለምትበላው ለሲምበግዊሬ የሚደርሳት አልባሌ ነገር ነበር። በየምሽቱ ሲምበግዊሬ ወደ እንቅልፏ የምትሄደው እያለቀሰች ነበር፤ የእናቷን ብርድልብስ እያቀፈች ትተኛለች።

6

አንድ ቀን ጠዋት ሲምበግዊሬ ተኝታ አረፈደች። ‹‹አንቺ ሰነፍ!›› ስትል አኒታ አምባረቀችባት። ሲምበግዊሬን ጎተተቻት። ያን ውድ ብርድልብስ ምስማር ያዘውና ከሁለት ተቀደደ።

7

ሲምበግዊሬ በጣም ተበሳጨች። ከቤት ለመጥፋት ወሰነች። የእናቷን ብርድልብስ ቁራጮች ይዛ፣ ጥቂት ስንቅ ቋጠራ ቤቱን ለቃ ሄደች። አባቷ የሄደበትን መንገድም ይዛ ጉዞዋን ጀመረች።

8

ሲመሽባት ከአንድ ምንጭ አጠገብ ካለ ትልቅ ዛፍ ላይ ወጥታ ከቅርንጫፎቹ ላይ መኝታዋን አዘጋጀች። እየተኛችም ሳለች ‹‹ እናቴ፣ እናቴ፣ እናቴ፣ ተውሽኝ። ተውሽኝና አልመለስ አልሽ። አባቴ አሁን ለኔ ማሰቡን ተቷል። እናቴ፣ መቼ ነው የምትመጭው? ተውሽኝ እኮ›› በማለት አዜመች።

9

በቀጣዩ ማለዳ ሲምበግዊሬ ዘፈኑን ደግማ ዘፈነችው። ሴቶች ልብሳቸውን ለማጠብ ወደ ምንጩ ሲመጡ ከትልቁ ዛፍ የሚመጣውን የመከፋት ዘፈን ይሰሙ ጀመር። ንፋሱ ቅጠሉን እያማታ የሚፈጥረው ድምጽ መስሏቸው ስራቸውን ቀጠሉ። ከሴቶቹ አንዷ ግን ዘፈኑን በጣም በጥንቃቄ አደመጠችው።

10

ይህች ሴት ቀና ብላ ዛፉን አየች። ልጅቱንና የብርድልብሱን ቁራጭ ስታይ ‹‹ሲምበግዊሬ ፣ የወንድሜ ልጅ!›› ስትል ጮኸች። ሌሎቹም ሴቶች ማጠባቸውን አቁመው ሲምበግዊሬን ከዛፉ እንድትወርድ አገዟት። አክስትዮዋም ትንሿን ልጅ አቅፋ ታጽናናት ጀመር።

11

የሲምበግዊሬ አክስት ልጅቱን ወደቤቷ ወሰደቻት። ለሲምበግዊሬም ትኩስ ምግብ ሰጠቻት፤ የእናቷን ብርድልብስም አለበሰቻት። በዚያ ምሽት ሲምበግዊሬ ወደ መኝታዋ ስትሄድ አለቀሰቸ። እንባዋ ግን የእፎይታ እንባ ነበር። አክስቷ እንደምትንከባከባት አውቃለች።

12

የሲምበግዊሬ አባት ወደቤቱ ሲመለስ ቤቱን ባዶ አገኘው። ‹‹ምን ተከሰተ አኒታዬ?›› አላት ክብድ እያለው። ሲምበግዊሬ መጥፋቷን ነገረችው። ‹‹እንድታከብረኝ ስፈልግ ነበር›› አለች። ‹‹ምናልባት ከረር አድርጌባት ሊሆን ይችላል።›› የሲምበግዊሬ አባት ቤቱን ጥሎ ወደ ምንጩ በኩል ሄደ። ሲምበግዊሬን አይታት እንደሆነ ለመጠየቅም ወደ እህቱ መንደር ዘለቀ።

13

ሲምበግዊሬ ከአክስቷ ልጆች ጋር እየተጫወተች ሳለች አባቷን ከሩቅ አየችው። ይናደድብኛል ብላ ፈራች። ስለሆነም ለመደበቅ ወደቤቱ በኩል ሮጠች። አበቷ ግን ወደሷ ሮጦ ‹‹ሲምበግዊሬ ጥሩ እናት አግኝተሻል - የምትረዳሽና የምትወድሽ። እኮራብሻለሁ፤ እወድሻለሁ›› አላት። ሲምበግዊሬ ከአክስቷ ጋር እስከፈለገችበት ጊዜ ደረስ እንድትቆይም ተስማሙ።

14

አባቷ በየቀኑ ይጠይቃት ጀመር። አንድ ቀንም ከአኒታ ጋር መጣ። አኒታም ሲምበግዊሬን ለመጨበጥ እጇን ዘረጋች። ‹‹ልጄ አዝናለሁ፤ ተሳስቻለሁ›› በማለትም አለቀሰችባት። ‹‹እንደገና አንድ ዕድል ትሰጪኝ?›› ሲምበግዊሬም አባቷንና የተጨነቀ ፊቱን አየች። ከዚያም በኋላ ቀስ ብላ ወደፊት ጠጋ አለችና አኒታን አቀፈቻት።

15

በቀጣዩ ሳምንት አኒታ ሲምበግዊሬን ከአክስቷና ከልጆቿ ጋር በቤቷ ምሳ ጋበዘቻቸው። ምን ዓይነት ግሩም ድግስ ነው! አኒታ ሲምበግዊሬ የምትወዳቸውን ምግቦች ሁሉ ስላሰናዳች ሁሉም ሰው እስከሚጠግብ ድረስ በላ። ከዚያም አዋቂዎቹ ሲያወሩ ልጆቹም ተጫወቱ። ሲምበግዊሬም ደስተኝነትና ጀግንነት ተሰማት። በቅርቡ፣ በጣም በቅርቡ፣ ወደቤቷ እንደምትመለስና ከአባቷና ከእንጀራ እናቷ ጋር እንደምትኖር ወሰነች።

16
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ሲምበግዊሬ
Author - Rukia Nantale
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Benjamin Mitchley
Language - Amharic
Level - Read aloud