በሬ እና አህያ
Melese Getahun Wolde
Salim Kasamba

አንድ ድሃ ገበሬ አንድ መሥራት የማይወድ ያረጀ በሬ ነበረው፡፡ በሬው የባለቤቱን መሬት ማረስ አይፈልግም ነበር፡፡ የሚፈልገው እቤት ውሎ ሳር መብላት፣ ውሃ መጠጣትና ማረፍ ብቻ ነበር፡፡

1

"ገበሬው አንድ አህያም ነበረው፡፡ አህያውና በሬው ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን በሬውና አህያው ተወያዩ፡፡ በሬውም "እኔ በጣም ደክሞኛል፣ቀኑን ሙሉ እሰራለሁ፡፡ ማረሻው ትልቅና ከባድ ነው፡፡ ጌታዬም በፍፁም እንዳርፍ አይፈቅድልኝም" አለ፡፡."

2

"አህያውም በሬውን ትኩር ብሎ አየው፡፡ "ይኸ በሬ ሰነፍ መሆን አለበት፣ መሥራት አይወድም" ብሎ አሰበ፡፡ ከዚያም እንዲህ ሲል በሬውን ጠየቀ፤ "ማረሻው ከባድ ነው ብለህ ታስባለህ? ጓደኛዬ እመነኝ፣ ማረሻው በጣም ቀላል ነው! እኔ ዛሬ ኩንታል ጤፍ በጀርባዬ ስሸከም ነው የዋልኩት፡፡ እርግጠኛ ነኝ አንተ ከምትለው ማረሻ የኔ ሸክም ይከብዳል" አለው፡፡."

3

በሚቀጥለው ቀን ሁለቱ እንስሳት እንደገና ተገናኙ፡፡ በሬው እንዲህ አለ፤ "የዛሬው ቀን ለኔ መጥፎ ነበር፡፡ የጌታዬ የእርሻ ቦታ ሩቅ ነው፤ ደግሞም ድንጋይ የሞላበት ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ስሰራ ነበር የዋልኩት፡፡ ምንም ዕረፍት የሚባል ነገር አልነበረኝም" አለ፡፡."

4

አህያውም እንዲህ ብሎ ጠየቀ "ጠንክረህ ስትሰራ ዋልክ? እኔ ዛሬ ብዙ ኪሎሜትሮች ርቆ ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ገበያ ሄጀ ነበር፤ እርግጠኛ ነኝ ካንተ የበለጠ ሠርቻለሁ" አለው

5

በሚቀጥለው ቀን በሬው ወደ ቤት ዘግይቶ መጣና "ኦ! ጓደኛዬ! ዛሬ ለኔ በጣም መጥፎ ቀን ነበር" አለው፡፡ ነገርግን አህያው በሬውን ከዚያ የበለጠ ሊያዳምጠው አልፈለገም ነበር፡፡

6

ከዚያም " አንተ ሁልጊዜ ይደክምሃል፤ እያንዳንዱ ቀን ላንተ መጥፎ ቀን ነው፡፡ አዳምጠኝ! አንድ ጥሩ ሀሳብ አለኝ፡፡ ነገ ጌታህ ገበሬው ሲመጣ መሬት ላይ ተጋድመህ ዓይኖችህን ጨፍንና ሟ… ሟ… በል፡፡ ገበሬውም የታመምክ ይመስለውና እንድታርፍ ይፈቅድልሃል" አለው፡፡ በሬውም የአህያውን ሀሳብ ወደደውና "አመሰግናለሁ ውድ አህያ! ይህ በጣም ጥሩ ሀሳብ ነው" አለ፡፡

7

በሚቀጥለው ቀን ጧት በሬው መሬት ላይ ተጋደመ፡፡ ገበሬውም ሲመጣ ዓይኑን ጨፈነና ‹‹ሟ… ሟ…›› አለ፡፡ ገበሬውም ተመለከተውና "አይ! ይኸ ሽማግሌ በሬዬ ታሟል፣ ግን እርሻዬን የግድ ማረስ አለብኝ፤ ማን ሊረዳኝ ነው? አሃ! ለምን? አህያዬ አለ ለካ፤ ዛሬ እሱ ማረስ ይችላል›› አለ፡፡

8

ከዚያም ገበሬው አህያውን ወደማሳው ወሰደና ማረሻና ቀንበሩን በአህያው ላይ ጠምዶ ሂድ! ፍጠን! ጎትት! እያለ በአለንጋ ይገርፈው ጀመር፡፡

9

አህያውም ቀኑን ሙሉ ጠንክሮ ሲሠራ ውሎ ወደማታ ላይ በጣም ደከመው፡፡ ከዚያም ቀስ ብሎ ወደቤቱ እያዘገመ ተመለሰ፡፡ በሬውም ጠበቀውና "ውድ ጓደኛዬ አህያ! ዛሬ በጣም ደስ የሚል ቀን ዋልኩኝ፤ ጥቂት ሳር በላሁ፣ ውሃም ጠጣሁና ከትልቁ ዛፍ ሥር አረፈኩኝ፡፡ ነገም እንደገና ማረፍ እፈልጋለሁ፣ ምን ላድርግ? እስቲ ሌላ ዘዴ ስጠኝ" ሲል ጠየቀው፡፡

10

አህያውም በሬውን ተመለከተውና "የሱ ሥራ ከኔ በጣም የከፋ ነው፤ ነገ እንደገና ይህን ሥራ መሥራት አልፈልግም!" ሲል አሰበ፡፡ ከዚያም "ጓደኛዬ! በጣም መጠንቀቅ አለብህ፣ዛሬ ገበሬው ከሚስቱ ጋር በሬዬ ሁልጊዜ ይደክመዋል፣አሁን ደግሞ አሞታል፣ ነገ ካልተሻለው አርደዋለሁ፤ ሥጋውንም መብላት እችላለን" እያለ ሲያወራ ሰምቸዋለሁ አለው፡፡

11

በሬውም በጣም ፈራና "ምን? እንደዚያ አለ? ስለዚህ ነገ እሠራለሁ፣ አሁን በጣም ተሽሎኛል፣ ምንም ድካም አይሰማኝም" ብሎ ጮኸ፡፡

12
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
በሬ እና አህያ
Author - Melese Getahun Wolde, Elizabeth Laird
Illustration - Salim Kasamba
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs