ኖዚቤሌና ሦስቱ ጸጉሮች
Tessa Welch
Wiehan de Jager

በድሮ ጊዜ ሦስት ሴቶች እንጨት ለመስበር ከቤታቸው ወጥተው ነበር።

1

ሞቃት ቀን ስለነበር ለመዋኘት ወደ ወንዝ ወረዱ። ተጫወቱ፤ ውኃ ተራጩ፤ ዋኙ።

2

ድንገት መምሸቱን ተገነዘቡ። ወደ መንደራቸውም ተጣደፉ።

3

እቤታቸው ሊደርሱ ሲሉ ኖዚቤሌ እጇን አንገቷ ላይ አደረገች። የአንገት ጌጧን ረሳታዋለች! ‹‹እባካችሁ አብራችሁኝ ተመለሱ!›› ብላ ባልንጀሮቿን ለመነቻቸው። እነሱ ግን በጣም እንደዘግየች ነገሯት።

4

ስለዚህ ኖዚቤሌ ወደ ወንዙ ብቻዋን ተመለሰች። የአንገት ጌጧንም አግኝታ ወደ ቤቷ ለመመለስ ተቻኮለች፤ ነገር ግን በጨለማ ውስጥ ጠፋች።

5

ከሩቅ ከአንዲት ጎጆ የሚወጣ ብርሃን አየች። ወደሱም ሄዳ በሩን አንኳኳች።

6

ባልተጠበቀ ሁኔታ ዉሻ በሩን ከፈተላት። ‹‹ምን ፈልገሽ ነው?›› አላት። ‹‹ጠፍቻለሁ ፤
እና ማደሪያ ቦታ ፈልጌ ነበር›› ብላ ነገረችው። ‹‹ነይ ግቢ፤ አለዚያ እነክስሻለሁ!›› አላት ዉሻው። ስለዚህ ኖዚቤሌ ገባች።

7

ከዚያም ዉሻው ‹‹ምግብ አብስዪልኝ!›› አላት። ‹‹እንዴ፣ እኔ እኮ ለዉሻ ምግብ ሰርቼ አላውቅም››
ብላ መለሰችለት። ‹‹ስሪልኝ፤ አለዚያ እነክስሻለሁ!›› አላት። ስለዚህ ኖዚቤሌ ለዉሻው ምግብ ሰራችለት።

8

ከዚያም ዉሻው ‹‹አልጋዬን አንጥፊልን! አላት። ኖዚቤሌም ‹‹እኔ እኮ ለዉሻ አልጋ አንጥፌ አላውቅም››ብላ መለሰችለት። ‹‹አንጥፊልኝ፤ ያለዚያ እነክስሻለሁ!›› አላት ዉሻው። ስለሆነም ኖዚቤሌ
አነጠፈችለት።

9

በየቀኑ ለዉሻው ምግብ መስራት፣ ማጽዳትና ማጠብ ስራዋ ሆነ። ከዚያም አንድ ቀን ዉሻው ‹‹ኖዚቤሌ፣ ዛሬ ጓደኞቼን ልጠይቅ እሄዳለሁ፡፡ እኔ ከመምጣቴ በፊት ቤቱን አጽጂ፤ ምግብ ስሪ፤ የሚተጣጠቡትንም ነገሮች እጠቢ›› አላት።

10

ዉሻው እንደሄደ ኖዚቤሌ ከራሷ ላይ ሦስት ጸጉሮችን ነቀለች። አንዱን ጸጉር ከአልጋው ስር፣ አንዱን ከበሩ ኋላ እና ሌላውን ደግሞ በከብቶቹ በረት አስቀመጠቻቸው።

11

ዉሻዉም እንደተመለሰ ኖዚቤሌን ፈለጋት። ‹‹ኖዚቤሌ፣ የት ነሽ?›› ብሎ ተጣራ። ‹‹አልጋው ስር ነኝ›› አለ የመጀመሪያው ጸጉር። ‹‹በሩ ጀርባ ነኝ›› አለ ሁለተኛው ጸጉር። ‹‹በረት ውስጥ ነኝ፣›› አለ ሌላኛው ጸጉር።

12

ከዚያም ዉሻው ኖዚቤሌ እንዳታለለችው ገባው። ስለዚህ ወደ መንደሩ እየተሯተሯጠ ፈለጋት። የኖዚቤሌ ወንድሞች ግን ትላልቅ ዱላዎች ይዘው እየጠበቁት ነበር። ውሻው ተመልሶ ሮጠ፤ ከዚያም በኋላ በመንደሩ በጭራሽ ታይቶ አያውቅም።

13
You are free to download, copy, translate or adapt this story and use the illustrations as long as you attribute in the following way:
ኖዚቤሌና ሦስቱ ጸጉሮች
Author - Tessa Welch
Translation - Mezemir Girma
Illustration - Wiehan de Jager
Language - Amharic
Level - Longer paragraphs